Print this page

ኤርትራውያን ሰላማዊ ሰልፈኞች ለዶር. ኣብይ ኣሕመድ ያቐረቡት መልእኽት

2018-11-01 07:33:43 Written by  ሰላማዊ ሰልፍ ኣዘጋጅ ኮሚተ Published in ጽሑፋት ትግርኛ Read 2589 times
Rate this item
(0 votes)

ለተከበሩ ዶክተረ ኣብይ ኣህመድ

የኢትዮጵያ ፈደራላዊ ደሞክራስያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስተር

ሰላምና ጤና ኣይለዮት፡

እኛ ዜሬ ከፊትዎ የቆምነው፣ የሰላማዊ ሰልፍ ተሳታፊዎች፣ ዲሞክራሲ፣ መልካም ኣስተዳደር፣ የፍትህ ልዕልናና መልካም ጉርብትና የምንመኝ ፣ ነገር ግን ኤርትራ ባለው ብልሹ ኣስተዳደርና ጭቆና ምክንያት ከምንወዳቸው ህዝባችንና ኣገራችን ተለይተን በመላው ዓለም ተበታትነን እየኖርን ያለነው ኤርትራውያን ነን። ሰላማዊ ሰልፋችን እርስዎን ለመቃወም የተዘጋጀ እንዳልሆነ ተገንዝበው፣ ኣዳማጭ ነዎትና፣ ቅሬታችንና ጥሪያችን ለዘላቂ ሰላምና፡ ለኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦች መልካም ጉርብትና የሚመለክት ነውና ፣ ነተገቢውን ትኩረት ያደርጉለት ዘንድ ክብርነትዎን ለማስታወስ መሆኑን በትህትና እንገልጻለን።

በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው፣ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች መፍታት፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ኣገራቸው ገብተው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንዲወዳደሩ መፍቀድ፣ የወጣቶችና የሴቶች የኣመራር ሚና ማጐልበትና ሌሎች የለውጥ እርምጃዎችን ከልብ የምንደግፋቸውና የምናደንቃቸው ናቸው።

በኤርትራና በኢትዮጵያ የተፈረመው፣ የኣልጀርሱ ስምምነትና የደንበር ኮምሽኑ ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብለው፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ መሃል ሰላም እንዲሰፍን ለወሰዱት እርምጃ እንደ መርህ የምንቀበለውና የምንደግፈው እርምጃ ነው። ለዚሁ ለወሰዱት እርምጃ ስንታገል መቆየታችንም ያለፈው ልምዳችን የሚመሰክረው ነው። ይህንኑ እርምጃዎ ተገባራዊ ይሆን ዘንድ ግን፡ ብመጀምርያ ደረጃ በሁለቱ ኣገሮች ወይ መሪዎች የተደረሰው ስምምነት ለሁለቱ ኣገራት ህዝቦች ግልጽ መሆን ይነሩበታል ባዮች ነን።

የሁለቱ ሃገራት ድንበር ስለ መከለል፣

ድንበርን በግልጽ መከለል፣ መሰረታዊ የሰላምና የመረጋጋት፣ የህዝቦች የክብርና የማንነት መለያ፣ እንዲሁም የኣገሮች የሉኣላውነት ማሳያ መሆኑ፣ በሚገባ የምትገነዘቡት ነው። ይቅርና ኣገሮች ትናንሽ መንደሮችም ቢሆኑ የየራሳቸው ድንበር ኖሩዋቸው ነው ተግባብተውና ተጋግዘው በሰላም የሚኖሩት። ስለዚህ፡ ድንበር ሳይከለል በሰላም ለመኖርና ሆነ መልካም ጉርብትና ለመመስረት ኣስቸጋሪ ስለሚሆን፣ ይህኑ ግምት ውስጥ ገብቶ የድንበር መካለል ጉዳይ ለኛ ሁለተኛ ደረጃ ሳይሆን፣ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሰራበት ተገቢ ነው እንላለን። የኤርትራም የኢትዮጵያም ልኡላውነት የሚታወቀው ድንበራቸው ሲከለል ነው። ስለዚ መጭው የኤርትራና የኢትዮጵያ ትውልድ በኣጠቃላይ፣ ወጣቶቻችንን ደግሞ በተለይ ድንበራቸው ግልጽ የሆነና ልኣላዊነታቸው በግልጽ የተረጋገጡ ኣገሮች እንድናስረክባቸው፣ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ግልጽ ስምነቶች እንድትዋዋሉላቸው ታሪካዊ ግዴታና ሃላፊነት እንዳለብዎት ማስታወስ እንፈልጋለን። ይህንኑ ተግባራዊ ካደረጉ ታሪክዎ በሁለቱ ኣገሮች ህዝቦች የማይረሳ ሆኑ ይመዘገባል።

ስምምነት ከማን ጋር

ኤርትራ ሕገ መንግስታና ሕገ-መንግስታዊ ኣስተዳደር ከሌላቸው ኣገሮቭች ኣንዷ ናት። ኤርትራ ህዝብዋ የሚያውቀና የተሳተፈበት ህጋዊ ተቋማት የላትም። ከዚህ ኣንጻር የኤርትራ ህዝብ በኣንባገነናዊ ጨቋኝና ኣሸባሪ ቡድን መንጋጋ እየኖረ ያለ ህዝብ ስለመሁኑ እርስዎን መንገር ኣስፈላጊ ኣይደለም። ምክንያቱም ኤርትራ ያለው ግፍ ሞልቶ ወደ ውጭ በመፍሰሱ የጐረቤት ሃገር ህዝቦችም የተሰቃዩበትና የደሙበት ነው። ይሁን እንጂ ያለፈውን ችግር እንዳለ ሆኖ፣ ሰላም ሰፍኖ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ለመገናኘት መቻላቸው የሚጠላ ባይሆንም፣ ለዚህ ሁኔታ ያበቁ ስምምነቶች በህዝባችን የማይታወቁ መሆናቸው፣ ለሚቀጥለው ትውልድ ችግር እንደሚፈጥሩ ልናስታውስዎት እንፈልጋለን። ምክንያቱም በኤርትራ ህዝብ ስም ከርስዎ ጋር ስምምነት እየፈረመ ያለው የኢሳይያስ ኣፈወርቅ ስርዓት፣ እርስዎን እንደወከለ መንግስት ተቁማዊ ኣሰራር የሌለው ስለ ሆነ። እርስዎ ጋር እየተፈረሙ ያሉ ስምምነቶች፣ ይቅርና የኤርትራ ህዝብ፣ ለስሙ የካብኔ ኣባላት የሚባሉትም የሚያውቁትና የተወያዩበት ኣይደለም። ከዚህ ኣንጻር እነዚህ ስምምነቶች እንዴት ነው ዘላቂ ሰላም የሚስገኙ? ከኣሁን በፊት በኤርትራና በኢትዮጵያ በረሃዎች፣ እንዲሁም ብ1992 በኤርትራና በኢትዮጵያ መሃከል የተፈረመው ህዝብ የማያውቃቸው ወተሃደራዊና ጸጥታዊ ስምምነቶች ከፍተኛ እልቂት ወዳስከተለ ጠርነት እንደወሰዱን የሁለቱ ህዝቦች የቅርብ ትዝታ ነው። የኤርትራ ህዝብ ምን ያህል በጨቋኝ ኣምባገነናዊ ኣስተዳደር እንደተበደለ የሁለቱ ኣገራት ድንበር ሲከፈት ወደ ኣገርዎ እየጐረፈ ያለው የኤርትራ ህዝብ ብዛት መረጋገጫ ነው።

ስምምነት ብማን እማኝነት

በኣሁኑ ግዜ በኣረብ ሰላጤ ኣገሮችና ብኣፍሪቃ ቀንዲ ያለውን ሁኔታ ለሚከታተል ታዛቢ፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ የተፈጠረው ደም ኣፋሳሽ ጦርነት እንዲቆም ብሃሳብ ኣፍላቂነት ከሚጠቀሱ የኣፍሪቃ ሃገራት ብርኪናፋሶና ኣልጀርያ ተጠቃሽ ናቸው። ይባስ ብሎ የኣፍሪቃ ህብረት ዘንግቶ ሳውዲ ዓረብያ ላይ የሚደረግ ስምምነት፣ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ብማይመለከታቸውና በማያውቁት የዓረቦች የሃያልነት ውድድር ውግያ ኣካል እንዳይሆኑ ያለንን ስጋት ልንደብቆው ኣንፈልግም።

ቅጥ ያጣ የንግድ እንቅስቃሴ

የኤርትራና የኢትዮጵያ ድንበር ከተከፈተ ቀን ጀምሮ፣ እየተካሄደ ያለው መርህ ኣልባ የንግድ እንቅስቃሴ፣ ለግዜው የኤርትራ ህዝብ የመሰረታዊ ኣቅርቦት ጥያቄ የመለሰ ቢሆም፣ ነገ ወደ ኣላስፈላጊ ኣቅጣጫ ሊወስድ እንደሚችል የሚያጠራጥር ኣይደለም። ለ1998 የኤርትራና ኢትዮጵያ ጦርነት ዋና መነሻው ኤኮኖሚ እንደነበር የሚዘነጋ ኣይደለምና። ስለዚ እየተካሄደ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ወደ ሌላ ጦርነት የሚያመራ እንዳይሆን፣ የንግድ ስርዓቱ የሁለቱ ኣገሮች ሉኣላዊነት በጠበቀ መልክ የማስያዙ ሃላፊነት እንደሚጠበቅብዎት ማስገንዘብ እንወዳለን።

ሞራላዊና ሰብኣዊ ግዴታ

በኤርትራ ህዝባችን ኣደጋ ላይ ጥሎ የቆየውና ኣሁንም በዚሁ ጨቋኝ ኣካሄዱ እየቀጠለ ስላለው ስርዓት ተገቢው ግንዛቤ ስላለን፣ ይህንኑ ስርዓት ለመገርሰስ በመረባረብ ላይ ነን። ኤርትራ ላይ ኩለንተናዊ ለውጥ እውን የሚሆን በባለቤቱ ብኤርትራ ህዝብ ትግል ቢሆንም፣ እርስዎም የኤርትራ ህዝብ እስረኞቹ እንዲፈቱለት፣ ተቃዋሚዎች ህጋዊ በሆነ ኣገባብ ኣገራቸው ገብተው የሚወዳደሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚፈቅድ ስርዓት እንዲመሰረት ሞራላዊና ሰብኣዊ ሚናዎ የመጫወት ሃላፊነት እንዳለብዎት ማስታወስ እንፈልጋለን።

በመጨረሻ ላይ ፣ የኤርትራ ህዝብ ያልጠበቀው ኣስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞት፣ እናቶች ከህጻናትና ወጣት ከልጆቻቸው ጋር በመሰደድ ላይ ናቸው። የኤርትራ ህዝብ ኢትዮጵያ ሲደርስ በህዝቡ መልካም ወንድማዊ ኣቀባበል እየተደረገለት ስለ ሆነ እናመሰግናለን። ይሁን እንጂ ኣቀባበሉ ከህዝቡ ኣቅም በላይ ሊሆን ስለሚችል፣ ህዝባችን በመንግስትዎ ደረጃ የትምህርት ዕድልና የጤና እንክብካቤ ያገኝ ዘንድ ትብብርዎ እንዳይለየው በትህትና እንጠይቃለን። የህዝባችን ደህንነት እንዲጠበቅም እንዲሁ እናሳስባለን።

ወንድማማችነትና መልካም ጉርብትና ይለምልም

ሰላም ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች

ኤርትራውያን የሰላማዊ ሰልፍ ተካፋዮች

ፍራንክፈርት ጀርመን

ጥቅምት 31 2018

Last modified on Thursday, 01 November 2018 08:42